ሃይማኖት ፤ ሃይመነ አሳመነ ፡ ካለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ፤ ትርጉሙም በአንድ አምላክ ማመን ለአንድ አምላክ መታመን ማለትን ይገልጻል ።
ሃይማኖት፣ እምነትና መታመን
ሃይማኖት
ሃይማኖት እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጅ የገለጠው መግለጥ ነው፡፡ እግዚአብሔር ባሕርዩ ረቂቅ አኗኗሩ ምጡቅ ስለ ሆነ የሰውም ሆነ የመላእክት አእምሮ ተመራምሮ ሊደርስበትና ባሕርዩ እንዲህ ያለ ነው፣ አኗኗሩ ይህ ነው ወይም ይህን ይመስላል ሊለው የማይችል ነው፡፡ እርሱ በጊዜና በቦታ የማይወሰን ዘለዓለማዊና ምሉዕ ሲሆን ፍጥረት በሙሉ ደግሞ በጊዜና በቦታ የተወሰነ ስለ ሆነ ውስኑ የማይወሰነውን ሊያውቀውና በምርምር ሊደርስበት አይችልም፡፡
ሆኖም ግን ምንም እንኳ እግዚአብሔር ባሕርዩና አኗኗሩ በራሱ ብቻ የሚታወቅ ረቂቅ አምላክ ቢሆንም እኛ ፈጽሞ የማናውቀውና ስለ እርሱ ምንም ፍንጭ የሌለን ሆነን እንድንቀር አልተወንም፡፡ ከቸርነቱ የተነሣ ዓቅማችን ሊረዳው በሚችለው መጠን ማንነቱን፣ ህላዌውን፣ ባሕርዩን፣ መግቦቱን፣ ፈታሒነቱን፣ ፈቃዱን፣ … እናውቅ ዘንድ በተለያየ መንገድ ገልጦልናል፡፡ ሃይማኖት የሚባለው ይህ እግዚአብሔር በራሱ ፈቃድ እናውቀው ዘንድ ስለ ራሱ የገለጠው መገለጥ ነው፡፡ ስለሆነም ሃይማኖት እግዚአብሔር ራሱን ለእኛ ያሳየበት መንገድ፣ የሰው ልጅ ሊቀበለው በሚችለው መጠን ስለ ራሱ ማንነት ለእኛ የገለጠው እውነታ ነው፡፡ ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ “የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል” እንዳለ፡፡ ዮሐ. 16፡12-13
እግዚአብሔር አንድ ስለ ሆነ፣ ባሕርዩም የማይለወጥ ስለ ሆነ፣ ሃይማኖት (ይህ አምላክ ስለ ራሱ የገለጠው መግለጥ) አንድና የማይለዋወጥ ነው፡፡ ስለዚህም ሊኖር የሚችለው እውነተኛ ሃይማኖት አንድ ብቻ ነው፡፡ ብዙ ሃይማኖቶች አሉ ማለት ግን፣ ወይ እግዚአብሔር በተለያየ ጊዜ የተለያየ ነገር ይናገራል ማለትን፣ አለዚያም ደግሞ ባሕርዩ ይለዋወጣል ማለትን ያስከትላል፤ ሆኖም እነዚህ አስተሳሰቦች ለእግዚአብሔር ሊነገሩ ቀርቶ ሊታሰቡ የማይገባቸው ጸያፎች ናቸው፤ እርሱ በተለያየ ጊዜ እርስ በእርሱ የሚቃረን የተለያየ ነገር አይናርምና፣ ባሕርዩም አይለዋወጥምና፡፡ መለወጥ የፍጡር ባሕርይ እንጂ በእግዚአብሔር ዘንድ መለወጥ የለም፡፡ ስለዚህ ሃይማኖት አንድ ብቻ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት” የሚለው ለዚህ ነው፡፡ ኤፌ. 4፡5 እንዲሁም ሐዋርያው ቅዱስ ይሁዳ “. . . ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ” በማለት ሃይማኖት አንድ ጊዜ ከእግዚአብሔር ለቅዱሳን የተሰጠ መሆኑን በአጽንዖት ገልጿል፡፡
ይሁዳ 3
እንዲሁም ለሃይማኖት መታዘዝና መጠበቅ ይገባል፡፡ “የሰይጣን ዙፋን ባለበት የምትኖርበትን አውቃለሁ፤ ስሜንም ትጠብቃለህ፥ ሰይጣንም በሚኖርበት፥ በእናንተ ዘንድ የተገደለው የታመነው ምስክሬ አንቲጳስ በነበረበት ዘመን እንኳ ሃይማኖቴን አልካድህም” በማለት ሃይመኖቱን ሳይክድ በመጠበቁ አመስግኖታል፡፡ ራእ. 2፡13 ቅዱስ ጳውሎስም “መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፣ ሩጫዬን ጨርሼያለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄያለሁ” በማለት፤ እንደዚሁም “እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፣ ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ” በማለት ሃይማትን መጠበቅ እንደሚገባ በጽኑ አሳስቧል፡፡ 2 ጢሞ. 4፡7 ዕብ. 4፡14

